Print this page
Wednesday, 15 June 2022 10:38

በስፋት አድጓል በጥራት በኩል ግን...

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝሙርና የዝማሬ አገልግሎት ከየት ወዴት?

ከአዲሱ ወርቁ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ፦

ከድምፀ ማህሌት መፅሄት ቁ. 1፣ 2004 የተወሰደ

  

1. ሙሉ ስም፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች

ስሜ አዲሱ ወርቁ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የማመልከው ሎስ እንጀለስ በምትገኘው የኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከመደራጀቷ በፊት የጥቂት ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስ የማጥኛና የመነቃቂያ ህብርት ከነበርንበት ጊዜ አንስቶ ነበርኩኝ፡፡ ከዚያም ጥቂት ወገኖች በመተባበር ቤተ ክርስቲያኒቱን ጌታ ረድቶን አደራጅተን ያኔ ከባለቤቴ ከሄላገነት በኋላም ከሁለት ልጆቼ ከጽዮንና ከማህሌት ጋር እያመለክን በአባልነትና፣ በመዝሙር አገልግሎት እንዲሁም አንዳንዴ ከመሪዎች አንዱ በመሆን ጌታ በሰጠኝ ዕድልና ብርታት አብሬ እስካሁን ተጉዣለሁ፡፡

2. ወደ ዝማሬ አገልግሎት እንዴት ገባህ? አገልግሎት በጀመርክበት ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እንዴት ነበር?

ጌታን በተቀበልኩበት ዘመን ወደ ጌታ የመጣሁባት እናት ቤተ ክርስቲያኔ የሙሉ ወንጌል ቤተ አማኞች ቤ/ክ አዘውትራ ልጆቿን ታስተምር የነበረው ስለመመስከር ሲሆን ሁሉም አማኝ አገልጋይ የሚል መርህ ነበራት፡፡ ሁሉም አባል ጌታ ለምን አገልግሎት እንደሚፈልገው ለማወቅ በሚጥርበት ጊዜ አንዳንዶች ወደ ወንጌላዊነት፣ ሌሎችም ወደሌላው ሲሄዱ እኔም በአቅሜ ዝንባሌዬን ዳስሼና መክሊቴ ነው ብዬ ስላመንኩበት በመዝሙር ለማገልገል የግል እርምጃ ወሰድኩ፡፡ በመቀጠል በመጀመሪያ ከአንዳንድ አብረን ከምናመልካቸው ወገኖች ጋር አልፎ አልፎ መዝሙር ማቅረብ ጀመርን፡፡ ከዚያም እማርበት በነበረው በወቅቱ የንግድ ሥራ ት/ቤት (Commercial School) አሁን ግን የንግድ ሥራ ኮሌጅ በሚባለው ውስጥ አዳሙ አባት ከሚባል ወንድም ጋራ የመንፈሳዊ ክበብ አቋቁመን በዚያው ሰበብ የንግድ ሥራ ት/ቤ መዘምራን ከመሰረትን በኋላ እድል ባገኘንበት ስፍራ እየተዘዋወርን ማገልገል ጀመርን፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የሙሉ ወንጌል ሀ መዘምራን በሚመሰረትበት ጊዜ አባል እንድሆን ቤ/ክ ባቀረበችልኝ ጥሪ መሰረት የመዘምራኑ አባል በመሆን በመደበኛ የቢተ ክርስቲያን የመዝሙር አገልግሎት ውስጥ ተሰማራሁ፡፡

አገልግሎት በጀመርኩበት ዘመን ያለው ሁኔታ በአጠቃላዩ የወንጌላዊያን አቢያተ ክርስቲያን በነፃነት እንዲያገለግሉ የሚያበረታታ አልነበረም፡፡ በተለይ እኔ አመልክባት የነበረችው የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤ/ክ ላይ የከፋ የስደት ዘመን ነበረ፡፡ ይኸውም ደርግ ከመምጣቱ በፊት ማለት ነው፡፡ የስደቱ መልክም መደብደብን፣ ንብረት መቀማትን፣ ከቤተሰብና ከመኖሪያ፣ ከትምህርትና ከሥራ ገበታ መባረርን፣ የውጭ አገር የትምህርት እስኮላርሺፕ መነጠቅን፣ ውስጥ እግር መገረፍን፣ መታሰርንና ሞትንም እንኳን ያካተተ ነበረ፡፡ ከመዘምራንም አንዳነዶቻችን የተጠቀሱትን አንዳንድ ጽዋዎች ቀማምሰናል፡፡ የወንጌል ሥራው ግን ሳይገታ እየበዛና እየጠነከረ የሚያምኑትም እየጨመሩ ይሄዱ ነበር፡፡

 

 

 

3. መዝሙርንና የዝማሬን አገልግሎት እንዴት ትገልጸዋለህ?

በመጠኑ እንደተረዳሁት መዝሙር አንድ አማኝ አምላኩን እንዲያመልክበትና በቅኔ ራሱንና ሌላውን እንዲያንጽ አማኝ ለሆነ ሁሉ ከአምላካችን የተሰጠን ልዩ የመገናኛ መስመር ነው ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ባለቤትነቱም የግለሰብ ወይም የግለሰቦች ሳይሆን የጌታና የቤተ ክርስቲያኑ ነው እላለሁ፡፡ አንድ ግልሰብ ከጌታ አንድ መዝሙር ቢቀበል ወይም ቢሰጠው ለአካሉ እንዲየስተላለፍና አካሉ እንዲታነጽ ነው፡፡ የመዝሙሩ ተቀባይና አስተላላፊ (ደራሲ እንደሚባለው ማለት ነው) በመዝሙሩ በኩል የሚመጣውን ማንኛውንም በረከት አብሮ እየተካፈለና እያገለገለ ከአካሉ ጋራ ይታነጻል ያድጋልም፡፡ የአካል ክፍል ያለአካሉ አያድግም፤ የሆነ ቢመስል ግን ጤና አይደለም፡፡ የጌታ ቃል ስጦታን ለቤ/ክ ሰጠ ይላልና እኔም እንደ አካሉ አንድ ብልት በእኔ የተቀመጠው ስጦታ የግሌ ድርሻ ቢኖረኝም የአካሉም ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ እንደማንኛውም የወንጌል አገልግሎት የመዝሙር አገልግሎትም የጌታን ክብርና የመላ አካሉን ጥቅም ያማከለ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ነው የመዝሙሩ ባለቤት አካሉና (ቤተ ከርስቲያን) የአካሉ ራስ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ማለቴ፡፡

ቃሉ እነደሚያስገነዝበን አገልግሎት በመጀመሪያ መሆን እንጂ ማድረግ አይደለም፡፡ ጌታ ኢየሱስም ደቀመዛሙርቱን በዚህ መንገድ ነው ያሰማራቸው፡፡ መጀመሪያ ራሳቸው መሆን የሚገባቸውን ሆኑ፣ ከዚያ እነሱ የሆኑትን ሌሎች እንዲሆኑ እንዲያስተምሩ ተልከው ወጡ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሳያምንበትና ሳይኖርበት መጽሐፍ ቅዱስን ከፍቶ ለሌላው የሚናገር፤ ምንም ያህል ችሎታ ቢኖረውና ቢያደርገውም የቃሉ አገልጋይ ብለን ካልጠራነው መንፈሳዊ ቃልን ከሙዚቃ ጋር አቀናብሮ የሚያቀርብ ነገር ግን የሚዘምረውን የማያምንበትና የማይኖርበት በእውነት የመዝሙር አገልጋይ ነው ማለት እንችል ይሆን፡፡ አገልጋይ ሁሉ ድካም ቢኖርበትም ቅሉ አገልጋይ ከመባል የሚከለክል የድክመት ገደብ ግን አለ፡፡ በጌታ አገልግሎት ላይ የሚሉትን ሆኖ መገኘትና ቢያንስ ለመሆን መጣር ያስፈልጋል ምክንያቱም በክርስትና አገልግሎት መልካም የህይወት ምስክርነት የግድ ነው፡፡ ስለዚህ አገልጋዪ አገልግሎቱ ሳያገለግል ሰባኪ ስብከቱን ሳይሰብክ ዘማሪ መዝሙሩን ሳይዘምር የዕለት ምግባሩ ብቻውን ስለማንነቱና ስለየአገልጋይነት ብቃቱ መልካም ሊናገርለት ወይም ሊመሰክርለት ይገባል፡፡

የመዝሙር አገልግሎትን አሰራርና ሂደት በተመለከተ የምለው ጥቂት ነው፡፡ በአጠቃላይ የክርስቶስ ቤ/ክ አሰራር ልዩ ልዩ የአገልገሎት ክፍሎች አሉት፡፡ እነዚህም አገልግሎቶች ለአንድ አላማ በመቆም በመጣመር፣ በመደጋገፍ፣ በመጣጣምና በመመጣጠን እንዲካሄዱ ያስፈልጋል፡፡ የመዝሙር አገልግሎትም እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ክፍል በዚሁ መንገድ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በግልም ሆነ በጣምራ (በኳየር) መልክ የሚቀርብ የመዝሙር አገልግሎት በጌታ ቃል የተደገፍ፣ የአካሉን ጤንነት የሚገነባ፣ የቤተ ክርሰቲያንንም የበላይነት ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ይህን ስል አንድ አገልጋይ በአንድ ቤ/ክ ውስጥ ከአንድ አመራር ስር ሳይሆን ለማገልገል አይገባውም ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደምንረዳው የግል አገልጋይም ሆነ የጋራ አገልጋይ የመጨረሻ አድራሻው አካሉ ነው የአካሉም ራስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ የመዝሙር አገልጋይ በበለጠ ራሱን በመንፈሳዊ ጤንነት ለመጠበቅና ለማሳደግ፣ በበለጠ ለራሱም ሆነ ለተገልጋዮች ጠቃሚና ዘለቄታ ያለው ፍሬ ለማስገኘት፣ በዚህ ሁሉም ጌታን በበለጠ ለማክበር ካሰበ ራሱን የአንድ ቤተ ክርስቲያን አካል አድርጎ መመላለስና ማገልገል በጣም ይበጀዋል፡፡

 

4. በዝማሬ አገልግሎትህ በዋናነት ይገጥምህ የነበረ ተግዳሮት ምን ነበር? እስከ ዛሬ ለመቀጠል የረዳህ ነገር ምንድን ነው?

በመጀመሪያዎቹ የአገልግሎት አመታቴ ቤተ ክርስቲያን ላይ ይዘንብ ከነበረው ስደት እኔም ላይ አንዳንድ ጠብታዎች ከመድረሳቸው በስተቀር ሌላ የተለየ ውጫዊ ተግዳሮቶች አልገጠሙኝም፡፡ ከመዝሙር አገልግሎት ጋር በተያያዘ በዚያ ዘመን ዘማሪ ወይም የወንጌል አገልጋይ ለመሆን የሚነሳ ሁሉ ማጣትና ስደት ዱላና እስራት የሚታጨዱበት እንጂ ዝናና አድናቆት ማግኘትና ድሎት የሚለቀሙበት እንዳለነበረ የተረዳ ብቻ ነበር፡፡ ወጣትነትና የፖለቲካውም ውዝዋዜ የራሱን ግፊት ሳይሞክር አላላፈም፡፡ ነገር ግን ጌታ ካስቻለ ይቻላልና ታልፎ እዚህ ተደርሷል፡፡ ከአገርም ከወጣሁ በኋላ ስለጌታ ታማኝነት የዘመርኳቸወን ቃላቶች ዞር ብዬ በጎሪጥ ያየሁባቸው ቀናት እንደነበሩ አልክድም፡፡ ከዚያ ሸለቆ በኋላ ግን እነሱ እኔን የታዘቡኝ ነው የመሰለኝ፡፡ እስከዛሬ ለመቀጠል የረዳኝ አምላኬ ራሱ ሲሆን በቀደሙት የእምነት አባቶቼና እናቶቼ ምክርና ፍቅር በኩል ብዙ ደግፎኛል፡፡ አንዳንዴም ከአንገት በላይ አደምጥ ከነበሩት ዘመን እያለፈ ሲሄድ ግን እንደዕንቁ እየወደድኳቸውና እየጠቀሙኝ ከሄዱት ምክሮች አንዳንዶቹ ከሚቀጥለው ውስጥ ይገኛሉ፡፡

  • በመጀመሪያ ከሁሉም በላይ ክርስቲያን መሆኔንና ሌላው ትርፍ መሆኑን መገንዘብና በዚያ ቅደም ተከተል አገልግሎትን ማየት
    በጨቅላ ዘመኔ ከጌታ ጋር የገባሁት ቃልና በልቤ የተጻፈ ለጌታም እስከመጨረሻ ትንፋሼ አገለግልሃለሁ ብዬ የገባሁትን ቃል በየእለቱ ማስታወስ
  • መታዘዜ እንጂ በመድረክ መቆም ፋይዳ እንደሌለው መረዳት
  • ጌታ የሰጠኝ አገልግሎት ወይም መክሊት የእርሱ እንጂ የእኔ ስላይደለ መልሼ የምሰጠውም ስለሆነ የራሴ ብዬ እንዳልቆጥረው ራስን በየጊዜው ማሳታወስ
  • ከአካሉ ጋራ ቢመቸኝም ባይመቸኝም አብሬ ልጓዝ፣ ለቤተ ክርስቲያን ታዛዥ መሆን፣ ቀድመውኝ ያገለገሉትንና ለወንጌል የደከሙትን ማክበር፣ ምክር መጠየቅ፣ ከነሱ መማር፣ ግንኙነት መቀጠል
  • ተስፋ ከሚያሰቆርጥ ይልቅ አድናቆትን መፍራትና መከላከል - ተስፋ የሚያስቆርጥ ያጠወልጋል አድናቆት ግን ከተመቻቹለት ከሥር የሚነቅል ሃይል አለው
  • በተለይ የመዝሙር አገልግሎት ለሥጋ ፈተና/ለግል ዝነኝነት የተጋለጠ ስለሆን ነቅቶ ህይወትን መጠበቅ

5. በአንተ አስተያየት አንድ ዘማሪ መዝሙር የሚጽፈው ወይም የሚቀበለው እንዴት ነው?

የእያንዳነዱ የመዝሙር አገልጋይ የተለያያ ልምድ ስላለው መንገዱ ይህ ብቻ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በግሌም እንኳን እንደተለማመድኩት በአንድ መንገድ ብቻ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ አንዳንዱ ባልታወቀ መንገድ በውስጤ ተቀርጾ ስዘምር ራሴን ያገኘሁበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ ምስጋና ምሰጋና ለኢየሱስ ምስጋን የሚለውና ክቡር ክቡር ኃያል ክቡር የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለጌታ የምናገረው (ምስጋናም ሆነ ልመና) በኖረኝ ጊዜ የልቤን አውጥቼ እንደደብዳቤ ጽፌ ወደመዝሙር የተለወጡ አሉ፡፡ ለምሳሌ ባንተ አምላኬ ብዙ አልፌአለሁ፣ የእግዚአብሔር በግ የሆንከው፡፡ በግንዛቤም ያለግንዛቤም ለምሳሌ በሕልምም እንኳን መዝሙር ይሰጣል፡፡ ከዚህም በላይ በሰው ጥበብ ሊገለጽ በማይቻል ባልተለመደ መንገድ የጌታ ሃሳብ በሰው አንደበት በዝማሬም የሚገለጽበት ጊዜ እንዳለ ከልምድ ተምሬአለሁ፡፡

6. ከዛሬ ሃያ አመታት በፊትና በዚህ ዘመን በሚዘመሩ መዝሙሮች መካከል የምታያቸው ጉልህ ልዩነቶች ምንድናቸው?

ዘመን እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሚከተሉት ነገሮች እየተለወጡና እየጨመሩ የመጡ ይመስለኛል፡፡ አብዛኛዎቹ መዝሙሮች በመልዕከታቸውም ሆነ በአገልግሎቱ ስምሪት ወደ ግላዊነት እያመዘነ መምጣቱ፣ የመዝሙሮቹ ሃሳብና መልዕክት አንዳንዴ ቃል በቃል ተወራራሽነት፣ የአንዳንድ መዘሙሮች ቃላት ከላባ የቀለሉ፣ ሲብስም ከጌታ ቃል ጋር የማይስማሙ መሆናቸው፣ የብዙዎቹ መዝሙሮች ሙዚቃዎች ቃናና አደራደር ደግሞ አንዱ የሌላው መዝሙር ቀጥታ ግልባጭ እየሆነ መሄድ፣ ቃሉም ሆነ የዜማው ቅላፄ ብዙ ምዕመን በአንድነት ለመዘመር የሚያዳግተው እየሆነ መምጣቱ፣ መዝሙር በአምልኮ ስም የመዝናኛ መሳሪያ ሆኖ የዘፈን ወንበር ላይ መቀመጡና የዘፈንን ፕሮገራም መተካቱ፣ መዝሙር ጉልበት ከማጣቱ የተነሳ ከሃዲውም ተቃዋሚውም ቢዘምረው የማይቆጠቁጠው እየሆነ መሄዱ፣ የመዝሙሩ ቃላት መሃል ሰፋሪ መሆን ማለትም የማይስብ የማይገፋም መሆኑ፣ የመዝሙር ሲዲዎችን ከማከፋፈልና ከመሸጥ እንዲሁም ከግል አገልጋዬች እየተዘዋወሩ ከሚያገለግሎት ጋር በተያያዘ የብር ማግኘት ተጽዕኖ፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም ያጠቃልላል፡፡

በሌላው አንጻር ደግሞ እየተሻሉ የሄዱም ነገሮች አሉ፡፡ የአገልገሎቱ ስፋት የአገልጋዮች ብዛት፣ በልዩ ልዩ የአገር ቋንቋዎች መዝሙሮች መጻፋቸውና መዘመራቸው፣ ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን መጠቀም፣ የሙዚቃ እውቀት መጨመር፣ ከመዘምራን የወጡ አድገው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች የሆኑ እየበዙ መሄድ፡፡ በምኖርበት አገር የማይታይ፣ በአገር ቤት ግን ብዙ መልካም ነገር እንዳለ አደምጣለሁ እገምታለሁም፡፡

7. የመዝሙር አገልግሎት አሁን የደረሰበትን ደረጃ ስትመለከት እንደሚገባ አድጓል ትላለህ?

በስፋት አድጓል በጥራት በኩል ግን ተጨማሪ ሥራ ይጠብቀናል። ጥራት የምለው የመዝሙር ቃሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊነት፣ አገልግሎቱን አሰጣጥ፣ የአገልጋዩን የሕይወት ምስክርነት፣ የመዝሙር አገልግሎትን በተለይም የግል ዘማሪዎችን ከቤተ ክርስቲያን ሌሎች አገልግሎቶች ጋር በቅርበትና በመጣመር አበሮ መስራት፣ ይህንና የመሰሉትን ነገሮች በተመለከተ ነው፡፡ በአጠቃላይ አንጻሩ ግን አዎንታው ከአሉታው ይበልጣል፡፡

8. የዚህ ዘመን የዘማሪያን ተግዳሮቶች ምን ምን ይመስልሃል?

ስለራሴ ካለሆነ በቀር ስለሌላው በይመስለኛል መናገሩ የሚያሰፈራ ነገር ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ተግዳሮቶቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ የአገልጋዩ የትውልድ እድሜ፣ የክርስትና የኑሮና የትምህርት ደረጃ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መልክና መስክ የተግዳሮቱን አይነትና ጥንካሬ ይወስነዋል፡፡ በእለት እንጀራና የመዝሙር አገልግሎት በመስጠት መካከል የሚፈጠር ተግዳሮት አለ፡፡ ከሥጋም ሆነ ከመንፈሳዊ ወጣትነትን ተገን አድርጎ የሚገለጥ በተለይ አሰራርንና አመለካከትን አካል የሚያደርግም ትግል አለ፡፡ ከራስ ሳይሆን ከውጪ ከተመልካችና አድማጭ ይሁን ሳይባል ከሚተላለፍ ምላሽም ሆነ ሃሳብ በመነሳት ታዋቂነትን (celebrity) የመፈለግ ፈተናም አለ፡፡ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ስር ሆኖ ማገልገል ዲሲፕሊንን፣ ታዛዥነትንና፣ ራስንና የራስን መስጠትን፣ ከሌላው ጋር አብሮ መስራትን ስለሚጠይቅ አንዳንድ ጊዜ በፈለጉት መንገድ በሚፈልጉት ፍጥነት መጓዝን ያሰቸግራል፡፡ ይህም ለብዙዎች የግል ዘማሪዎች አይመችም፡፡

9. ለተሻለ እድገትና መልካም ለውጥ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

ለውጥ ከሁሉም አቅጣጫ ስለሚመጣና የሁሉንም ሃሳብ የተደመጠበት፣ የታየበትና የተመዘነበት ሊሆን ስለሚገባው አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳደግና ውጤታዊ ለማድረግ ከቀደሙት ብቻ ሳይሆን በዘመናችንም ከሚያገለግሉትም ጋር በአንድነት የምንወያይበት መድረክ ቤተ ክርስቲያን ብትፈጥር መልካም ይመስለኛል፡፡ የመዝሙር አገልግሎት ጥቅምም ሆነ ሳይፈለግ ተከትሎት የሚመጣው ጉዳት የአንድ አጥቢያ ቤት ክርስቲያን ወይም የእነድ ቤተ እምነት ሳይሆን የመላው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ነው፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱ ላይ መልካም ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልገው ጥረት በዚያ መልኩ መሞከር አለበት እላለሁ፡፡

10. ቤተ ክርስቲያን ለዝማሬ አገልግሎትና ለዘማሪያን ተገቢውን ትኩረት ሰጥታለች? ካልሆነ ምን መደረግ አለበት?

በምዕራቡ አለም የተገነዘብኩትና የተለማመድኩት ቢኖር ለዘማሪያን እንጂ ለመዝሙር አገልግሎት ብዙም በግሌ የሚያጠግበኝ ትኩረት ሲሰጥ አላየሁም፡፡ የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ ለዘማሪያኑም ቢሆን የሚሰጠው ትኩረት ወቅታዊና ፕሮገራማዊ እንጂ ለዘለቄታ የሚሆን መንገድ የሚቀድና የሚያስጠምድ መልክ ባለው መንገድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዘማሪያን በግል መልካም ነው በሚሉት መንገድ ሲሄዱ ይታያሉ፡፡

የመዝሙር አገልግሎትን ደግሞ መመልከት ያለብን በቅድሚያ ከአካሉ አንጻር ነው፡፡ የአገልግሎት መኖር ለአገልጋዩ ሳይሆን ለተገልጋዩ ነው፡፡ ዛሬም አገልጋይ የሚያገለግለው የወጣው ከትላንት ተገልጋይነት ከሆነ ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን ማደረግ ያለባት የሚመስለኝ አገልግሎት መስጠትን ከማስተማር ጎን ለጎንና እንዲያውም በቅድሚያና በይበልጥ ምዕመኑ ማንኛውንም አገልግሎት መርምሮ መቀበል እንዲችል ገለባውንም ከፍሬው እንዲለይ ማስታጠቅ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዛሬ ለሚዘምሩት የሚጠበቅባቸውን ከማሳወቅም ተጨማሪ ነገ ለሚወለዱት ዘማሪዎች የህይወትና የአገልግሎት መሰረት ይሆንላቸዋል፡፡

በተለይ የአገራችን የወንጌል ጉዞ ታሪክ በግልጽ እንደሚያሳየን የመዝሙር አገልግሎት በዘመናት ብዙ ፍሬ ያፈራና በመዝሙር የሚያገለግሉትም ልክ በሌላ አገልግሎቶች ውስጥ እንዳሉት የወንጌል አገልጋዮች አብረው ዋጋ የከፈሉበት ለጌታ ሥራ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገ አገልግሎት ነው፡፡ አሁን ግን የመዝሙር አገልግሎት በአብዛኛው ቤ/ክ የሚታየው እንደተለጣፊ የሌላ አገልግሎት ማሟያ፣ ማጠናከሪያ ሆኖም ማማሟቂያ ሆኖ ነው፡፡ ስለሆነም በመዝሙር ለማገልገል የሚያስፈልገው የሕይወት ብቃትም ሆነ ጥሪ በቅጡው ሲመረመር አይታይም፡፡ በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች በአብዛኛዎቹ አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ የመዘምራን አባላት ሲለዋወጡ ይታያሉ የአገልግሎታቸውም ዘመን በአመታት ሳይሆን በወራት ነው የሚቆጠሩት፡፡ ይህም በተለይ በህብረት መዝሙር አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ አንዳንዶችንም ከህብረት አገልግሎት ወደ ግል አገልግሎት፣ በአንድ በራስ ቤተ ክርስቲያን በቋሚነት ከማገልገል እየተዘዋወሪ ወደ ማገልገል እንዲሄዱ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

11. በመጨረሻ ልታስተላልፍ የምትፈልገው መልእክት ምንድን ነው?

ከላይ የጠቀስኳቸው ነጥቦች ከተወሰነ ልምምዴና ካየሁት የመነጨ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ከራሳቸው ልምምድና እይታ ከእኔ የተለየ እንዲያውም የኔን የሚቃረን የሚበልጥም ነጥቦች ሊኖሯቸው እንደሚችል ከመገንዘብም አልፌ ልክ ሊሆኑ ይችላሉ እላለሁ፡፡ ሆኖም ግን ሃሳቤን መግለጼ በነጥቦቼና በሚመስሏቸው ላይ ለመነጋገር በር ይከፍት ይሆናል ስለምል ተነፈስኩኝ፡፡

በመጨረሻ ለቀጣዩ አገልጋይ የምተወው የሚከተለውን ነው፡፡
ከዚህኛው ይልቅ እዚህ ላይ አተኩር

Read 1715 times Last modified on Wednesday, 15 June 2022 10:44