Print this page
Wednesday, 15 June 2022 10:39

የምእመናን ጸሎት ድጋፍ ሆኖኛል

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝሙርና የዝማሬ አገልግሎት ከየት ወዴት?

 ከፓስተር ታምራት ኃይሌ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ፦

ከድምፀ ማህሌት መፅሄት ቁ. 1 2004 የተወሰደ 

 

1. ሙሉ ስም፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች

ስሜ ታምራት ኃይሌ ይባላል ባለትዳርና የአንዲት ሴትና የሶስት ወንዶች ልጆች አባት ነኝ። በሳክራሜንቶ፣ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነኝ።

2. ወደ ዝማሬ አገልግሎት እንዴት ገባህ? አገልግሎት በጀመርክበት ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እንዴት ነበር?

ጌታንና ሰዎችን በዝማሬ ማገልገል የጀመርኩት በአውሮፓውያን አቆጣጠር 1974 ዓ.ም. ነው። አገልግሎት የጀመርኩበት ቤተክርስቲያንም ብርሃነ ወንጌል መጥምቃዊት ቤተክርስቲያን የሚባለውና በአዲስ አበባ የቀድሞው ቡልጋርያ ኤምባሲ መዞሪያ አካባቢ የሚገኘው ነበር።

አገልግሎት የጀመርኩት በመዘምራን ህብረት አባል በመሆን ሲሆን ወቅቱም የኢትዮጵያ አብዮት ሁለተኛ አመት ገደማ ነበር። አብዮቱ የቀድሞ መንግስት 60 ያህል ባለሥልጣኖችንና ንጉሡን በመረሸን “በድል ለመገስገስ” ዕርምጃ የጀመረበትና ውሎ አድሮም ቢሆን ቤተክርስቲያናትና ወንጌላውያን አማኞች ሌላ ዓይነት “የአብዮታዊ እርምጃ” ድግስ እየተዘጋጀላቸው እንደሆነ የሩቅ ጭምጭምታ የሚሰማበት ወቅት ነበር።

የመላ ኢትዮጵያ አብያተክርቲያናት ቁጥር ስንት ይደርስ እንድነበረ አሁን በእጄ መረጃ የለኝም። በአዲስ አበባ ግን በስድስት ያህል ቤተ እምነቶች ሥር ወደ 19 ያህል ፀሎት ቤቶች እንደ ነበሩ አስታውሳለሁ (የቁጥር ስህተት ቢኖር ይቅርታ!)።

የቤተክርስቲያኒቱ ሁኔታ ለተባለው፤ በየፀሎት ቤቶቹ እንደየቤተ ዕምነቱ የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶች ነበሩ። የአገልግሎት ልውውጥም ነበር። ሰባኪዎችና መዘምራን በየአጥቢያው እየተጋበዙ ያገለግሉ ነበር። ትልቅ ፍቅር ይታይ ነበር። ከላይ በጠቀስኩት የአብዮት ጅማሬና ስደትም እንደማይቀርለት ይወራ ስለነበር በቃሉ ለመመስረትና በፀሎት ለመታጠቅ ሁሉም ይተጋ ነበር። የምሥራች ድምጽ፣ የብሥራተ ወንጌል የሬድዮ ጣቢያዎችና የብርሃን መጽሄት እንደዚሁም አንዳንድ ግለሰቦች የሚያወጡዋቸው ጽሁፎች፣ የደረጄ ከበደና በኋላም ጥቂት ቆይቶ የተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙሮች፣ የመሠረተ ክርስቶስ፣ የሙሉ ወንጌል፣ የአማኑኤል ባፕቲስትና በኋላም የብርሃነ ወንጌል ቤተክርስቲያናት የሚያወጧቸው ዝማሬዎች እነኚህ ሁሉ ሕዝቡን ለመጪው ስደት ያዘጋጁ ነበረ። መልዕክቶች በስብከትም፣ በትንቢትም፣ በመዝሙርም፣ በሬድዮም፣ በካሴትም በጽሁፍም ብቻ በሁሉም መንገድ አይቀሬውን ስደት ያስታውሱና አይዟችሁ! እያሉ ያደፋፍሩ ነበረ። የተባለው ጊዜ ደረሰናም ከጥቂት የመካነ ኢየሱስና ከአንድ የቃለ ሕይወት (ጌጃ መሠረተ ህይወት) ቤተክርስቲያናት በስተቀረ ሁሉም ፀሎት ቤቶቻቸው በበታች ባለሥልጥናት ቀላል ትእዛዝ ለመዘጋት በቁ።

በወጣት ማህበር፣ በሴቶች ማህበር፣ በመፈክር፣ በኪነት ጭፈራ እየተላከኩና ሰበብ እየተፈለገ በየቀበሌው እስር ቤት አማኞችን ማጎር ተጀመረ። የቆረጠና የተዘጋጀ ሥሩን ጠቅልሎ የሰደደና በዓለቱ ላይ የተመሠረተ በመከራው ውስጥ ጸና። የደከመም ለመንሸራተት ዳዳው። እንግዲህ እኔ አገልግሎት በጀመርኩበት አካባቢ የቤተክርስቲያናት ሁኔታ ከሞላ ጎደል ይህን የሚመስል መልክ ነበረው።

3. መዝሙርንና የዝማሬን አገልግሎት እንዴት ትገልጸዋለህ?

የዝማሬውን አገልግሎት የምገልጠው

  • በመከራ ጊዜ መጽናኛና መጠቀሚያ
  • በድል ጊዜ ምስጋና
  • የእግዚአብሔርን ዙፋን በአምልኮ ማድመቂያ
  • የወንጌል ስርጭት መሣሪያ (የነፍሳት መጥሪያ)
  • የምዕመናን ሕይወት ማነጫ (መገንቢያ)
  • የፀሎትና የምልጃ ማቅረቢያ
  • በሠልፍ ጊዜ የመዋጊያ መሣሪያ             

በጠቅላላው በዜማ የተቀመመና የጣፈጠ የወንጌል ስብከት (ደረጀ ከበደ ከተናገረው) በማለት ነው።

4. በዝማሬ አገልግሎትህ በዋናነት ይገጥምህ የነበረ ተግዳሮት ምን ነበር? እስከ ዛሬ ለመቀጠል የረዳህ

ነገር ምንድን ነው?

በዝማሬ አገልግሎቴ የገጠመኝ ተግዳሮት (challenges) ብዙ አይደለም። አገልግሎቱ አድማሱን ሊያሰፋ ሲል ከተማሪነት መስመር ሊያውጣኝ ታገለ። ጌታ ሲከብርና መእመናን ከላይ በጠቀስኩት አስቸጋሪ ወቅት ሲጽናኑበት አየሁ የጀመርኩትን የከፍተኛ ሁለትኛ ደረጃ በኋላም የተግባረ እድ የሙያ ስልጠና መቀጥል እንደተሳነኝ አስታውሳለሁ። አእምሮዬ ለትምህረት የሰነፈ ባይሆነም ያለእረፍት በየቦታው በማገልገል ከቀለም ላይ ትኩረቴን ስለቀነስኩ ውጤቶቼ ዝቅ እያሉ ሄዱ ቢሆንም አቋርጬ አልወጣሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታ (extension) ከተመዘገብኩ በኋላ ግን ስደቱም ሲነሳ ህዝቡም በድንጋጤ ውስጥ ሲሆን ሁሉንም ትቼ የመጣ እስኪመጣ ድረስ ማገልገሌን ቀጠልኩ። ይህንንም ስለ ጉድለት አልልም ጌታን በማገልገል ማነስ ስለሌለ።

በኋላ ያየሁት ትንሽ ችግር የአገልግሎቱ ባህርይ- አጥብያ ቤ/ክርስያን እንደ አንድ ወንጌላዊ ልታሰማራው የምትችለው አይነት ስለነበረ ተከታይ እረኛ አልነበረኝም፡ ሁሉም ዘንድ አለሁ ግን የማንም አልነበርኩም። ይህም መንፈሳዊ ጥበቃ ከማጣት አንስቶ የምግብና የመጓጓዣ አስከማጣበት ድረስ ይሄድ ነበር። ጥቂት የተጠራቀሙ መዝሙሮችን ለካሴት ቅጂ እንዲሆን አዘጋጅቼ ለቤተክርስትያኔ ያውም በደብዳቤ ማመልክቻ እንኳ ባቀርብ አንድ “ባጀት የለንም” ሌላ ግዜ “የመቅጃ ስቱዲዮ አይገኝም” እንደገናም “ ሀላፊነት ወስዶ የሚያሰራም ሰው የለንም” እየተባለ መቅረቱን አስታውሳለሁ። በዚያ ዘመን የመዝሙርና የዘማሪው ጭምር ባለቤቱ ቤ/ክርስትያን እንደሆነ ነበርና የሚታመንው እምነቴ ዛሬ ተለውጦአል ማለቴ አይደልም። ግን ቤ/ክርስትያን መዝሙሩንና ዘማሪውንም ተቀብላ ማሰማራትም ከውጤቱ መጠቀምም አለመቻሏ ይገርመኛል።

እስከዛሬ ለመቀጠል የረዳህ ምንድን ነው? ከተባለ ያው ጸጋው ነው፡ የጥሪውን መነሻና የጥሪውን አላማ ማወቅ ረድቶኛል፡ የምእመናን ጸሎት ማበረታቻ ትልቅ ድጋፍ ሆኖኛል። ዝማሬዎቹ በሰዎች ሕይወት በመንግስቱ ስራና በአገርም ታሪክ ላይ ጥቂትም ቢሆን ድርሻ ነበራቸውና ያንን ውጤት ሳይ በአገልግሎቱ ለመቀጠል ያደፋፍረኝ ነበር። በጉባኤም ሲዘመር ከመናፍስት መውደቅ ጀምሮ የእግዚአብሔር ክብር እየመጣ የሰዎችን ህይወት ሲነካ የተነኩ ሰዎችም በግል በጉባኤም ደስታቸውን ሲገልጡ ስሰማ የበለጠ ተሰጥቼ ለማገልገል ያበረታኝ ነበር።

5. በአንተ አስተያየት አንድ ዘማሪ መዝሙር የሚጽፈው ወይም የሚቀበለው እንዴት ነው ?

ዘማሪ ዝማሬ የሚቀበለው በጉልበቱ ተንበርክኮ ሲጸልይ፣ በስርአት ቃሉን ሲያጠናና ሲማር የሌሎችን ዝማሬ ሲሰማና

በጉባኤም ሲያመልክ፣ በተለያዩ የህይወት ገጠመኞች ውስጥ ሲያልፍ፣ ረጅም ጉዞ ሲያደርግ፣ አንዳንዴም ተኝቶ ሳለ በህልም

(በራዓይ) በቤተክርስትያን፤ በግለሰቦች፤ በአገር ወይም በአለም ላይ አንድ ነገር ሲከሰት፣ ስምቶ ሲደሰት ወይንም ሲያዝን፣ በነዚህ በአንዱ ወይም በሁሉም ውስጥ ነው መዝሙር የሚሰጠው።

6. ከዛሬ ሃያ አመታት በፊትና በዚህ ዘመን በሚዘመሩ መዝሙሮች መካከል የምታያቸው ጉልህ ልዩነቶች ምንድናቸው?

ከሀያ አመታት በፊት ከነበረው የተለየ (ጉልህ ልዩነት)

ሀ. የዘማሪዎች ብዛት

ለ. የዝማሬዎች ብዛት

ሐ. የሙዚቃ መራቀቅ

መ. የስቱዲዮ ጥራት

ሠ. መዝሙሮች ከዘፈኑ አለም ድረስ ዘልቀው ሄደው ልቀው መደመጣቸው

ረ. ዘማሪዎችና ዝማሬዎቻቸው ከቤተክርስትያን ክትትልና እረኝነት ወጥተውና ርቀው መሄዳቸው

ሰ. የዜማ፤ የሙዚቃ፤ የቃላት ድግግሞሽ (አንዳንዴም ቃል አልባ ዜማ)

ሸ. የሙዚቃ ሪትም ተመሳሳይነት

ቀ. የመልዕክቶታቸው አንድ አይነት (ምስጋና አምልኮ ላይ ብቻ) ጉልሆቹ እነዚህ የመስሉኛል። የቀድሞው እንግዲህ የዚህ ተቃራኒ ነበር ማለት ነው።

7. የመዝሙር አገል ግሎት አሁን የደረሰበትን ደረጃ ስትመለከት እንደሚገባ አድጓል ትላለህ?

የመዝሙር አገልግሎት ከላይ እንዳልኩት በዘማሪና ዝማሬ ቁጥር ብዛት በሙዚቃና ስቱዲዮ ጥራት ባድማጭ ብዛት አድጓል ይህንን ዕድገት እንደቀጠለ በሌላውም እንዲሁ ቢሆን ደግ ነው።

8. የዚህ ዘመን የዘማሪያን ተግዳሮቶች ምን ምን ይመስልሃል?

በዚህ ዘመን የዘማርያን ተግዳሮት (challenge)

- የእውነተኛ መንፈሳዊ አባት ማጣት
- የእናት ቤ/ክርስትያን እረኝነትና ክትትል ማጣት (በኢኮኖሚ መደገፍያ ማጣት)           - ዝማሬውን የሚመራው የህዝብ ፍላጎትና ገበያው የመሆኑ አደጋ ጥቂቶቹ ይመስለኛል።

9. ለተሻለ እድገትና መልካም ለውጥ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

ለተሻለ እድገትና ለውጥ መደረግ ካለበት ውስጥ ዘማሪዎቹ የሚነሱባቸው አብያተ ክርስትያናት ገና ከመነሻው ከልጆቻቸው ጋር ተቀምጠው መወያየት። በአብያተ ክርስትያናት ህብረት ደረጃ አንድ የምክር ጉባኤ መጥራት ዘማሪዎች ቆየት ያሉቱ እርስ በርስ ተቀራርበው በመወያየት የአገልግሎቱን ብርቱና ደካማ ጎን መርምረው ብርቱውን ጠብቀው ደካማውን ጎን አርመው ወደፊት የሚሄዱበትንና ክኋላ ለሚከተሏቸው መልካም ምሳሌ የሚሆኑበትን አቅጣጫ መቀየስ።

እኛ ሁላችንም ከመተቸትና ከመንቀፍም እንደዚሁም አብዝተን ከማድነቅም ዝም ብለን በጸሎትና በምክክር ምርቱን ከግርዱ መለየት።

10. ቤ/ክርስትያን ለዚህ አገልግሎት ተገቢውን ትኩረት ሰጥታለች ወይ?

ለዚህ ጥያቄ ካላይ የዘረዘርኳቸው በኔ በኩል ለጊዜው በቂ ይመስለኛል።

11. ልታስተላልፈው የምትፈልገው መልእክት

እግረ መንገዴን ያልኩ ይመስለኛል። ዘማሪዎች እስቲ አንዳችን ላንዳችን ወንድም እህትና አባትም እንሁን። ዘመኑ ብዙ ክፉ ነገር አለበትና እስኪ እንፈላለግ፣ ከሁሉም ይልቅ ግን አጠገባችሁና በውስጣችሁ ካለ ጌታ ጋር ተያያዙ አብያተ ክርስትያንና እረኛም ይኑራችሁ። ተጠያቂነት (Accountablity) ለህይውቱም ለአገልግሎቱም ያበጀ ሰው ረጅም መንገድ በጤና እንደሚሄድ አስታውሱ።

ቃሉን ብሉ በጸሎት ተጋደሉና አገልግሎታችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠራ ይሂድና የታላቁ ተልዕኮ መሳርያ ሁኑ።

የአብያተ ክርስትያናት መሪዎች ተነሱና ልጆቻቹን ፈልጉ በፍቅር ያዙአቸው፣ ተንከባከቡአቸው። ዕንቁ የጠፋባት ሴት እርስዋ ተነስታ ቤትዋን ከጓዳ ጀምራ እስከ ሳሎን በመጥረግ እይደል ውድ ንብረቷን ፈልጋ ያገኘችው (ሉቃስ 15፤8-10)። ዘማሪዎች ከውድም ውድ ልጆቻችሁ ናቸው (የልጅ ርካሽ ባይኖርም)። ምዕመናንና ሌሎች “ጉዳዪ ይከነክነኛል” የምንል ሁላችንም እየጸለይን “ጌታ ሆይ” ስለዚህ ጉዳይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ እንበለው።

ለሙሴ መንገዱን ያስታወቀና ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን ያሳየ አምላክ ለዛሬዎቹ ለኛም መንገዱን ያሳየናል ያስተምረናልም።

 

Read 2140 times Last modified on Wednesday, 15 June 2022 10:43