Blog

Wednesday, 15 June 2022 10:46

ዕድገቱን ለማምጣት ምኑ ጋ ነው ያላደኩት የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝሙርና የዝማሬ አገልግሎት ከየት ወዴት?

ከጌታያውቃል ግርማይ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ፦

ከድምፀ ማህሌት መፅሄት ቁ. 1 2004 የተወሰደ

 

1. ሙሉ ስም፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች

ስሜ ጌታያውቃል ግርማይ ይባላል አጥቢያ ቤ/ክ በኢትዮጵያ መካነ የሱስ ቤ/ክ ሲሆን አሁን ደግሞ በኢሊኖይ፣ ሻምበርግ መካነ የሱስ ውስጥ ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ጋር እያገለገልኩ ነው።

2. ወደ ዝማሬ አገልግሎት እንዴት ገባህ? አገልግሎት በጀመርክበት ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እንዴት ነበር?

የዝማሬ አገልግሎትን የጀመርኩት የ 13 ዓመት ተኩል ልጅ ስሆን፣ የሻለቃ ግርማይ ሓድጎ እና የወንጌላዊት ጥሩነሽ  ቤተሰብ መዘምራን በሚባለው የቤተሰባችን የዝማሬ አገልግሎት ውስጥ እንዲሁም በመካነ የሱስ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ውስጥ ሲሆን ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲመጣ ከብሩክታዊት ጋር ማገልገል ጀመርኩ። እኔ ማገልገል በጀመርኩበት ዕድሜዬ ብዙውን የቤተ ክርስቲያንን ሁኔታ ማስተዋል የጀመርኩት እየቆየ ቢሆንም ስለ እዛ ዘመን ልናገር የምችለው ሁለት ነገር ቢኖር በዛን ዘመን የነበረችው ቤ/ክ ዝማሬን በጣም ትጠቀምበት እና ታከብር እንደነበረና ዘማሪያንም በትልቅ ፍርሃት እና መሰጠት ያገለግሉ እንደነበረ ብቻ ነው።

3. መዝሙርንና የዝማሬን አገልግሎት እንዴት ትገልጸዋለህ?

መዝሙር በሥነ ግጥም የተሰራ፣ በዜማ የታጀበ እና በጥሩ ቃና ባለው ስጦታውን በተላበሰ ሰው ለአምላክ ብቻ የሚቀርብ ማህሌት ነው ብዬ አምናለሁ። የዝማሬ አገልግሎት ግን በሁሉም አቅጣጫ ሥርዓትን ጠብቆ በቤ/ክ በኩል ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አገልግሎት ነው ብዬም አምናለሁ።

4. በዝማሬ አገልግሎትህ በዋናነት ይገጥምህ የነበረ ተግዳሮት ምን ነበር? እስከ ዛሬ ለመቀጠል የረዳህስ ነገር ምንድን ነው?

የዳዊትን ህይወት እንደምሳሌነት ብናይ በሁሉም ዘማሪ ፊት ለፊት የሚወረወር የጦር ፍላጻ አለ ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው። ተግዳሮት የሌለው የዝማሬ አገልጋይ እውነት የሚናገር አይመስለኝም። የተግዳሮቱ አይነት ግን ይለያያል። ከውጪ የሚላክ ተግዳሮት፣ ከኛው አለመጠንቀቅ እና አለማስተዋል የሚመጣ እንዲሁም በገዛ ራሳችን የምንፈጥረው ተግዳሮት ናቸው ብዬ አስባለሁ። እኔ እስከዛሬ ድረስ በዚህ አገልግሎት እንድቀጥል ያደረገኝ ትልቁ የእግዚአብሔር የጥሪው ጸጋ ብዛት ሲሆን በቅርቤ እና በአካባቢዬ ያሉ በበጎ መልኩ ምሳሌ የሆኑኝ እና በተለያየ መልኩ እያወቁትም ሳያውቁትም ያሳደጉኝ ሰዎች ናቸው።

5. በአንተ አስተያየት አንድ ዘማሪ መዝሙር የሚጽፈው ወይም የሚቀበለው እንዴት ነው?

መዝሙር በእንደዚህ ሁኔታ ውስጥ ስሆን ነው የምቀበለው የሚለው የተለያዩ ሰዎች አስተያያት መዝሙር ጽፎ የማያውቀውን ሰው ያንን የተናገሩትን አስተያያት በራሱ ላይ ለመመኮር ጥረት እንዲያደርግ ሲያስገድዱት ስላየሁ እና በእኔም ስለደረሰ ይህ አይነቱ አስተያየት ገና ወደዚህ አገልግሎት የሚገቡትን ይጠቅማቸዋል ብዬ አላስብም። ነገር ግን እንዴት ባለ ሁኔታ እንደምቀበል ሳይሆን እኔ መዝሙርን የምቀበልበትን የግሌን ዝግጅት እና ጉጉት መናገሩ ጠቃሚ ይመስለኛል። መዝሙርን በማንኛውም ሰዓት እና ሁኔታ ውስጥ ብሆንም ሁል ጊዜ ዝማሬን ለመቀበል የተዘጋጀ ማንነት ውስጥ መሆንን እመረጣለሁ። የሚመጡልኝን ዜማዎች በስልኬ ለመቅዳት የሚመጡልኝን የዝማሬ ሃሳቦች የምጽፍበት ነገሮችን ተሰናድቶ የመጠበቅ ልምዴን በየጊዜው የማስብበት እና የማደርገው ጉዳይ ነው። ሁሌ በንቃት ስለምጠብቀው ያ ሁኔታ ሲከሰት ፈጥኖ ለማስተናገድ ስለማልቸገር ማረፊያ እንደተዘጋጀለት አውሮፕላን ዝማሬው በላዬ ላይ አንዣቦ አይቀርም እኔ ላይ ለማረፍ ይገደዳል ብዬ አስባለሁ። ይህ ልምምድ በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ምክንያቱም በድንገት የሆነ አዲስ ዝማሬ ሲመጣ ፈጥኜ በመቀበሌ ብዙ ተጠቃሚ አርጎኛል።

6. ከዛሬ ሃያ አመታት በፊትና በዚህ ዘመን በሚዘመሩ መዝሙሮች መካከል የምታያቸው ጉልህ ልዩነቶች ምንድናቸው?

አንደኛው የመልዕክቶቹ ይዘት እንደየዘመኑ ለውጥ የማምጣት ግዴታ አለው ብዬ አስባለሁ። እንዲሁም ከቀድሞ ዘመን የምንጠቀምባቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች ሳይቀሩ ለውጥ ስላላቸው ሁለንተናዊ የሆነ ለውጦች እና ልዩነቶች አሉባቸው። ጉልህ የሆኑ ልዩነቶች ከምላቸው ውስጥ የአዘማመር ስልቶቻችን ከሙዚቃ፣ ከእንቅስቃሴ፣ ከመልእክቱ አይነት ማለትም ግላዊ ዝማሬዎች መበርከታቸው እንዲሁም ዜማዎቹ በአንድ የሜሎዲ ስኬል ላይ ማተኮራቸው ወዘተ ይመስሉኛል።

7. የመዝሙር አገልግሎት አሁን የደረሰበትን ደረጃ ስትመለከት እንደሚገባ አድጓል ትላለህ?

የመልእክት እና የዜማ እንዲሁም የሙዚቃዊ ጥበቦችን በተመለከተ እንዳጀማመራችን ዕድገታችን ብዙ አለመሆኑን ያሳያል። እንደውም በአንድ አዙሪት ላይ እንዳለ ነገር ድግግሞሽ በሁሉም አቅጣጫ ይታያሉ የሚለው ወቀሳ እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ ለዚህ መፍትሄው አገልግሎቱን ሥራዬ ብሎ መያዝ እና ማሳደግ መፍትሄው ነው ብዬም አስባለሁ።

8. የዚህ ዘመን የዘማሪያን ተግዳሮቶች ምን ምን ይመስልሃል?

አንዱን “ትንሽዬ ስኬት” ብዬ ስም አውጥቼለታለሁ። ለዘመናችን ዘማሪያን እኔንም ጨምሮ በሆነች የሰዎችን ልብ በምትነካ እና ጌታ እኛን ወደ አደባባይ ለመግለጥ እንደመነሻ አድርጎ ባስነሳት የሆነች አስደናቂ ዝማሬ ከታወቅን እሷኑ ይዘን ወደላይ ከነጠርን በኋላ በዛችው እንቀራለን። ጌታ ረድቷቸው ለሌላ ለተሻለ  ዝማሬ ራሳቸውን የሚያዘጋጁ እንዳሉ ሁሉ በባለፈው ጥጃ ወይም ዝና የዘንድሮንም እርሻ ለማረስ የሚክሩኩም አሉ። ለኔ ተግዳሮት ትናንሽ ስኬቶች ይመስሉኛል ብዙዎቻችን የምንታወቀው ብዙ በሰራናቸው ሳይሆን ጥቂት ባደረግናቸው መሆኑም ያሳስበኛል። በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ትዕቢቱን፣ገንዘብ ወዳድነቱን ወይም ለገንዘብ ደፋ ቀና ማለቱን፣ ከወጡበት ከፍታ ለመውረድ መታገሉን፣ ቅድስናን፣ ሥርዓት ማጣትን እና የመሳሰሉን ነቀፌታዎች እና ተግዳሮቶች በዚሁ እጠቀልላቸዋለሁ።

9. ለተሻለ እድገትና መልካም ለውጥ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

እንግዲህ ዕድገቱን ለማምጣት ምኑ ጋ ነው ያላደኩት የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል ምክንያቱም ብዙ ሰዎች የሰውነት ክብደታችውን ለመቀነስ እንቅስቃሴን ወይም የሰውነት ማጎልመሻ ጀምረው ጭራሽ ተቆልፎ የነበረውን የምግብ ፍላጎታቸውን የሚከፍቱ አሉ ይባላል። ስለዚህ እድገቱን ለማምጣት በምን ማደግ አለብን ብሎ ማሰቡ ቀዳሚ ይመስለኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እራሱ አገልግሎቱ አደገ ብለን የምንለካበት መለኪያ ካልተሰናዳ አሁን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አድጓል ብለው ስለሚያስቡ እሱ እራሱ መጣራት አለበት። ሰፊ ሃሳብ ስለሆነ በዚሁ ልግታው ሌላ ጊዜ በሰፊው በቀጠሮ ይያዝልኝ።

10. ቤተ ክርስቲያን ለዝማሬ አገልግሎትና ለዘማሪያን ተገቢውን ትኩረት ሰጥታለች? ካልሆነ ምን መደረግ አለበት?

ትኩረት የሰጡና አገልግሎቱን በሁሉም አቅጣጫ የሚያበረታቱ ቤተ ክርስቲያኖች እንዳሉ ማወቅ ይገባናል። በዛው መጠን ዘማሪ እና መዝሙር እንዳለ ትዝ የሚላቸው እሁድ ወይም አምልኮ ፕሮግራም ሲደረስ ብቻ የሆነም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶቹም ለመዝሙር ከፍተኛ ሥፍራ እየሰጡ ለዘማሪው የማይሰጡም ሊኖሩ ይችላሉ ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ አይንን የሚከፍት ውይይቶችና ሥልጠናዎች ሊደረጉ ይገባል ብዬ አስባለሁ። በዛውም መጠን ልካቸውን ወይም ጥጋቸውን ያለፉም አሰራሮች ስላሉ ልኩን ማስያዝ ያለብን ይመስለኛል።

11. በመጨረሻ ልታስተላልፍ የምትፈልገው መልእክት ምንድን ነው?

አንድ የምወደው በብዙ ነገር የጠቀመኝ ወዳጄ ያለኝን ብላችሁ ጥሩ መልዕክት ይወጣዋል። አንድ የታሸገ ውሃ በ2 ዶላር ገዛን ብንል ገንዘቡን የምናወጣው ለውሃው ነው? ወይስ ውሃው ላለበት ላስቲክ ነው? ወይስ ላስቲኩ ላይ ለተለጠፈው ውሃን ላሸገው ካምፓኒ ነው? አንዳንዶች እኔ ለውሃው ነው ይበሉ እንጂ ላስቲኩ የታሸገበት መክደኛ መከፈት ቀርቶ ላላ ካለ አዲስ አይደለም ብለው አይገዙትም። አንዳንዶች ለውሃው ነው ገንዘቤን ያወጣሁት ይበሉ እንጂ ላስቲኩ ላይ ያለው ውሃው የታሸገበት ካምፓኒ ስሙ ከሌለበት አይገዙትም። የዝማሬ አገልግሎት ልክ እንዲሁ ነው አለ ይህ ወዳጄ። ብዙዎች ዘማሪያን የምናተኩረው ውሃው ላይ ብቻ ይሆናል የምንዘምረው፤ መዝሙር ላይ ማለቱ ነው አንዳንዶቻችን ደግሞ የምናተኩረው የምናሳትመው ሲዲ፤ የውጪ ዲዛይኑ እና የተለጠፈብን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችን ስም እና የመሳሰሉት ሊሆን ይችላል። ሌሎቻችንም ዋናው የሙዚቃ ቅንብሩ ነው፣ ዜማው ነው፣ ግጥሙ ነው እያልን የውሃው ላስቲክ ክዳኑ ክፍት ሆኖብን ይሆናል፤ ባህሪያችን፣ አመላችን፣ የህይወት አካሄዳችንና እኛነታችንን የሚወክል ይመስለኛል። ስለዚህ ለውሃው ብቻ ሳይሆን ውሃው ላለበት ለታሸገበት ለተከደነበት ውሃውን የፈበረከው ማስታወቂያ ሳይቀር ሁሉ ነገር ተሟልቶ መቅረብ አለበት ወደ እንደዚህ አይነቱ ሁለንተናዊ ጥራት እግዚአብሔር ሁላችንን ያስገባን እላለሁ፤ አመሰግናለሁ።

ጌታያውቃል እና ብሩክታዊት

Read 1007 times

Mahlet Institute of Worship and Music
“Committed to Excellence in Worship and Music”

©2021 All rights reserved.