Blog

Wednesday, 15 June 2022 10:48

ያበረታታኝ ነገር ቢኖር ያገልግሎታችን ፍሬ ነው

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝሙርና የዝማሬ አገልግሎት ከየት ወዴት?

ከግዛቸው ወርቁ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ፦

ከድምፀ ማህሌት መፅሄት ቁ. 1 2004 የተወሰደ 

 

1. ሙሉ ስም፣ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች

ስሜ ግዛቸው ወርቁ ነው፡ የምኖረው ካሊፎርንያ ነው አሁን የማገለግልበት አጥብያ ቤ/ክርስትያ አቤኔዘር ይባላል በዛዙርያ ያሉትን ቸርቾችንም አግለግላሁ ብዙ ሰዎች የሙሉ አገልጋይ ፓስተር አርገው ያስቡኛል ግን የሙሉ ግዜ አግልጋይ  አይደሉም በሙያዬ ኤሌትሪካል ኢንጅነር ነኝ ከስራ ውጭ ጌታ በሰጠኝ ግዜና እንዲሁም አንዳንድ ግዜ ስራዬንም መስዋት በማድረግ አገለግላሁ ጌታን የምትወድ ባለቤት አለችኝ የባሌቤተስም መአዛ ይባላል ጌታም አብረን እናገለግላለን ጌታ የሰጠንም አንድ ወንድልጅ አለን።

2. ወደ ዝማሬ አገልግሎት እንዴት ገባህ? አገልግሎት በጀመርክበት ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እንዴት ነበር?

ጥያቄው በጣም ትልልቅና እና የተያያዘ ስፊ ትንተና የሚያስፈልገው ቢሆንም በተቻልኝ መጠን አሳጥሬ ለመመለስ እሞክራሁ። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ያደኩት መዝሙር በመስማት ነው ምክንያቱም ታልቅ ወንድሜ ዘማሪ አዲሱ ዘማሪ ነው ብስራት ወርቁንም ታውቁት እንደሆን አላውቅም እንዲሁም ደረጄ ከበደ ጎረቤታችን ነብር እና በነሱ ተከብቤ ነው ያደኩት። በዛ ወቅት እነሱ ጌታን ያውቃሉ ያገለግላሉ እኔ ግን ጌታንም ባላውቅ ቤ/ክርስትያን እሄድ ነበር ዋንኛ ቤ/ክርስትያንም የምሄድበት ምክንያት መዝሙር ለመስማት ነው። መዝሙርን መጀመርያ የሰማሁት በብስረተ ወንጌል ሬድዮ ነው የሰማሁትም የወንድሜን የአዲሱ ወርቁን ዝማሬ ነው። መዝሙር በጣም እወድ ስለነበር ከነሱ እየሰማሁ እዘምር ነበር። እንግዲህ በዚህ መሀል ጌታን ተቀበልኩ፤ ጌታንም በተቀበልኩበት ግዜ በጣም ልጅ ነበርኩ፤ የዘጠነኛ ክፈል ተማሪ ሆኜ፤ እርግጠኛ ባልሆንም የአስራ ሶስት ተኩል ወይንም የአስራ አራት አመት ልጅ እሆናለሁ። እንግዲህ ጌታን ከተቀበልኩ ግዜ ጀምሮ ብዙ መዝሙሮችን ጽፌአለሁ፤ ከጻፍኳቸው መዝሙሮች አንዱ በህይወት እስካለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፣ ለአምላኬ በዘመኔ ሁሉ እቀኛለሁ፤ ቃሌ ለሱ ይጣፍጠዋል ምስጋናዬም ደስ ያሰኘዋል፤ የሚል ነበር። ይሄን መዝሙር ኳየር ከመግባቴ በፊት የተቀብልኩት መዝሙር ነው። እንግዲህ በዛን ግዜ ኳየር በማመልከት ነበር የሚገባውና ኳየር ለመግባት በደብዳቤ አመለከትኩ፣ በዚያው ወቅት አካባቢ ስደቱም ተነሳና እስር ቤት ገባን ይሄ እንግዲህ የሆነው ወደ ሰባ አንዱ አመተ ምህረት መጨረሻዎቹ ላይ ነው።

ከእስሩ ስንፈታ ኳየሩ ወደኳየር እንድገባ አነጋገርኝ። በዛን ግዜ ኳየሩ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ብዙ ደስተኛ አልነበሩም ምክንያቱም ከንሱ መሀል እኔ በጣም ወጣት ነበርኩና። ቃል በቃል እኔን ለመጥራት የተጠቀሙበት ቃል ይሄ ጩጬ እንዴት ታስገቡታልችሁ ብለው ነበር። ለምንኛውም ገባሁኝ ብዙ መዝሙር እንድምጽፍም ማለቴ ጌታ እንደሰጠኝ አያውቁም ነበር። ነገር ግን ጌታ ጥሩ ጥሩ መዝሙሮችን ይሰጠኝ ነበር። እንግዲህ ድምጽ ሲታሰብ ከመጨረሻዎቹ መካከል ነው የምሰለፈው ግን ጥሪውና ጸጋው እንዳለኝ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ ምክንያቱም እኔ የማላስባቸውን ድንቅ ድንቅ መዝሙሮች በዛን ግዜ ጌታ እየሰጠኝ እጽፍ ነበርና ነው። አሁን የምትባረኩባቸው ብዙዎቹ መዝሙሮች የተጻፉት በዛን ግዜ ነው ለምሳሌ በካሴት ላይ ካልወጡ መዝሙሮች መሀል አዳም ሆይ ወዴት ነህ፤ ወዴት ልፈልግህ፤ አቤት አቤት ልበልና ልከተል፤ ድምጽህን ምናልባት ባገኝ። እነዚህ መዝሙሮች እንኳን ሌላውን እኔን ያስገርምኛል ይህ እንግዲህ የስኬትና ስንኝ የማገጣጠም ጉዳይ አይደለም ይህ የጥሪ እና የጸጋው ጉዳይ ነው። በዛን ገዜ የነበረው የስደቱ ወላፈን በጌታ ለመቆየት በጌታም ለመቆየት ከባድ ነበር። አብረውን ከታሰሩት ጌታን የተው አሉ በጣም ብዙ ነገርም ውስጥ ገባሁ ነገር ግን እንደዛ ነው ኳየር የጀመርኩት። በዛን ግዜ የነበሩትን የዝማሬዎችን ሁኔታ ስንመለከት መዝሙሮቹ የሚያመለክቱት እና የሚያንጸባርቁት የሰማዩን መንግስት ሁኔታ ነበር ስለዚህ ሞት የሚያስደነግጠን ሆኖ ለማንኛችንም አያስፈራራንም።

  1. መዝሙርንና የዝማሬን አገልግሎት እንዴት ትገልፀዋለህ?

በመጀመርያ የዝማሬ ምንነት ሀሳቡን ብንመለከት መልካም ነው። ዝማሬ ማለት ምን ማለት ነው? ለምንድነው የምንዘምረው? ዝማሬ ከሰማይ የወረደ ነው፤ የመላእክትንም ስራ ስንመልከት ኢየሱስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ በመለክት ዝማሬ ታጅቦ ነው የመጣው፤ ከማረጉ በፊትም ከራት በኋላ በዝማሬ ነው የተለያቸው። እንግዲህ ስለ ዝማሬ ሳስብ ሁለት ነገሮችን አስባለሁ። ዝማሬ ከሁለት አኳያ ውስጥ ከወጣ በኔ አስተሳሰብ ዝማሬ አይደለም ባይ ነኝ። ይህም ምንድን ነው? ዝማሬው ጸሎት ወይንም ወንጌል መሆን አለበት ከሁለቱ ከወጣ ዝማሬ አይደለም። ዝማሬ ግጥምም ሊኖረው ይችላል፡ በጸሎት ውስጥ ምስጋና ምልጃ እና ልመናን ያጠቃልላል። ወንጌልን በተመለከተ ደግሞ አዲሶችን የምንጠራበት፣ በጌታ ያሉትን የምናጸናበትና ከጌታ የሸሹትን የምንመልስበት ነው። ለምሳሌ ጌታ ይሻልህል፤ በኩርነትህን ለምን ሸጥከው፤ ልናርፍ ነው ወንድም ልናርፍ ነው እንዲሁም ሌሎችም። እኔ አገልግሎት በጀመርኩበት ግዜ የነበረው የዝምሬም ሆነ የወንጌል አገልግሎት የሚያነጥር ነው። ወይ ግባ ወይ ውጣ ነው መሀከል መሆን ቦታ የለውም።

  1. በዝማሬ አገልግሎትህ በዋናነት ይገጥምህ የነበረ ተግዳሮት ምን ነበረ? እስከዛሬ ለመቀጠል የረዳህስ ምንድን ነው?   

እኔ መዝሙር መዘመር የጀመርኩት፣ ፑልፒት ላይም መቆም የጀመርኩት መዝሙር መጻፍ በጀመርኩ ከአስር አመት በኋላ ነው ። በዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር አዋቂ ነው ምክንያቱም በዛን ግዜ ብወጣ ኖሮ እና ሰዎች ከፍ ቢያደርጉኝ ችግር ውስጥ ልገባ፣ ስዎች ቢነቅፉኝም ችግር ውስጥ ልገባ ስለዚህ በሁለቱም አልተርፍም ነበር ማለት ነው። ግን እግዚአብሔር ሸፈነኝ በተጨማሪም ጌታ በደንብ አርጎ አበሰለኝ እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲሆን ከጥቂቶች ሰዎች በቀር ብዙም የሚያበረታታ ሰውም አልነበረም ግን እግዚአብሔር ጥበብ ሰጠኝ ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ሳልደክም እንድቀጥል የረዳኝ ነገር ቢኖር ጌታን መውደዴ እና የጌታ ጸጋ ነው ምክንያቱም ጸጋ ያለው ሰው አይደክምም ስለዚህ ይህ ጸጋ አስቻለኝ ሐዋርያቶች ካንተ ወደማን እንሔዳልን እንዳሉት ከሱ ውጭ መሄጃ አለመኖሩን መረዳትም ከፍተኛ ብርታት ሰቶኛል። ሌላው ያበረታታኝ ነገር ቢኖር ያገልግሎታችን ፍሬ ነው። የእገልግሎታችን ፍሬ የሚታይ ፍሬ ነበረው በተለይ አንድ ግዜ፣ ተነስቷል የመቃብር ደጃፍ ተከፍቷል የሚለውን መዝሙር ታውቁታላችሁ ይህንን መዝሙር ጽፌ ለኳየር አቀረብኩ ኳየሩ ተለማመዱት። ከዛ በዛ በፋሲካ ግዜ ይዘምሩታል ብዬ ስጠብቅ አልዘመሩትም ልጅነትም ስለነበረ አልተዘመረም ብዬ በጣም አዘንኩኝ። በሚቀጥለውም አመት ስጠብቅ አልተዘመረም ይህ አንግዲህ የጌታ ፕላን እንጂ የሰዎች አይደለም ሶስተኛ ግዜ ይሄ መዝሙር እኮ ከተጻፈ ቆይቷል፣ ተዘምሮ አያውቅም ብላ አንዲት እህት አስታውሰች። በዚህን ግዜ እሺ ተባለና ተዘመረ ያንን ምሽት አስታውሳለሁ ቅዳሜ ማታ ለእሁድ አጥቢያ ነበር የተዘመረው ባጠቃላይ ሌሊቱን ሙሉ እሱ ተዘመረ። የኔ መዝሙር ስለሆነ ሳይሆን ግን በዚያን አዳር የነበረ የእግዚአብሔር መንፈስ እስከዛሬ አይረሳኝም። ስለዚህ አንዳንድ ግዜ መቼ እንደምንዘራ እና መቼ እንደምናጭድ አናውቅውም እንግዲህ እንደነዚህ መዝሙሮች ውጤቱን ስንመለከት ያበረታቱናል።

 

  1. በአንተ አስተያየት አንድ ዘማሪ መዝሙር የሚጽፈው ወይንም የሚቀበለው እንዴት ነው?

ያለጸጋ የፃፍነው ያለጸጋ ይቀራል፤ ምናልባት የጻፍነው መዝሙር ሰዎችን ደስ ሊያሰኝ ይችላል ግን ለመንፈሳዊ ህይወት ምንም አይጨምርም፣ ምንንም አይመልስም፣ የወደቀንም አያነሳም። ጌታ መዝሙርን ጸጋው ላለው ሰው በተለያየ መንገድ ይሰጣል። እኔ የራሴን ልምምድ ብንመለከት፥ ብዙ ግዜ መዝሙር የምጽፈው በጸሎት ላይ ሆኜ ነው። ለምሳሌ ጉልበቴ ሆይ የሚለውን መዝሙር የተቀበልኩት በጣልያን እያለሁ፣ በተለይ በአገልግሎቴ በብዙ ችግር ውስጥ ላይ በነበርኩበት ግዜ ነው። ስለዚህ ያ መዝሙር በሰው ቤት ውስጥ ተበርክኬ እንደተሰጠኝ ወንበሩን ሁሉ አስታውሳለሁ።በዛን ውቅት በቃ ተስፈ ልቆርጥ የነበረበት ሰአት ነበር ጌታ ግን አነሳኝ፣ ብድግም አደረገኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር በጸሎት መዝሙርን ይሰጣል። ሌላው በህልም የተሰጡኝ መዝሙሮች አሉ፣ አንዳንድ ግዜ ደግሞ ግዜ ሰጥቼ ጊታሬን ይዤ ቁጭ ባልኩበት ሰአት፣ መንገድ ላይ እና አምልኮ ላይ ሆኜ የተሰጡኝ መዝሙሮች አሉ። እንግዲህ በተለያየ መንገድ መዝሙርን ጌታ ይሰጣል መጽሐፍ ቅዱስ በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርኩ እንደሚል በመንፈስ በምሆንበት ግዜ ነው መዝሙር የሚሰጠን። ትልቁ ፈተና ምንድን ነው? እኛ መጻፍ የምንችል ይመስለናል እንሞክራለንም ግን አይደለም ደረጄ ከበደ መድረክ ላይ መዝሙር ከጌታ ተቀብሎ አዝማችና ቁጥሩን ዘምሮ መውረዱን በግሌ ነግሮኛል። ይሄ እንግዲህ እግዚአብሔር የሚሰጠው ጸጋ ይባላል። አንዳንድ ግዜ አዝማች ብቻ እንጂ ሙሉ መዝሙር ላይሰጠን ይችላል፤ ይህን ስል ግን ሙሉ መዝሙር የሚሰጥበት ግዜ የለም ማለቴ አይደለም። ለምሳሌ “አዎ ጌታዪ” የሚለው መዝሙር በ 1973 ዓ.ም. በስደቱ ግዜ፣ ብዙ ሰዎች ጸንተው ለመቆም በተቸገሩበት ግዜ የዚህ መዝሙር አንድ ቁጥር ብቻ ነበር የተጻፈው። ይህ መዝሙር፣ ኬንያ፣ ከአምስት አመት በኋላ ነው ተጽፎ ያለቀው። ስለዚህ አንደኛ፣ ያልተሰጠንን ለመጨረስ መታገል የለብንም ያለበለዛ የመዝሙሩ አንድ ቁጥሩ ሀይለኛ ይሆንና የቀረው ደግሞ ማለቅ አለበት ተብሎ የተጻፈ ይመስላል፣ መልእክቱም ደካማ ይሆናል። ይሄን ስናገር ወንድሞቼንና እህቶቼን ለመንቀፍ ሳይሆን ይህን ሁላችንም እንድረዳው ብዬ ነው። ሁለተኛ፣ ካሴት ለማውጣት ተብሎ አንደኛው መዝሙር በጣም ጥሩ ይሆንና ያ ወንድም ጸጋ የለውም፣ ዘማሪ አይደለም ማለቴ ሳይሆን አንደኛውን፣ ያቺን በጣም ጥሩ የሆነችውን መዝሙር ከጌታ እንደተቀበለ፤ ሁለተኛውንም መዝሙር ልክ እንደመጀመርያው ከጌታ ጋር ግዜ ወስዶ ቢጨርሰው ካሴቱ እንዴት ያማረ ይሆን ነበር? እንግዲህ ባጠቃላይ መዝሙር ልንቀበል የምንችለው በጌታ ፊት በመሆን እና በመንፈስ በመሆን ነው።

በመጨረሻ አንድ ነገር ብናግር ደስ ይለኛል፤ እኛ ዘማሪያን አንድ መጠንቀቅ ያለብን ነገር ቢኖር ደጋግመን የምንዘምረው መዝሙር እኛ የምንወደውንና ህዝቡ ይወደዋል ብለን የምናስበውን ነው። ጌታ ለዛ ህዝብ ምን አመጣ አይደለም፤ እዚህኛው ቸርች ዝማሬው ህዝቡ ከተባረከበት እዛኛው ጋ ለመዘመር ነጻንት ይሰማናል ሆኖም ግን መልእክተኛ መሆናችንን እንዳንረሳው መጠንቀቅ እንዳለብን ማሳሰብ እፈልጋለሁ።

  1. ከዛሬ ሀያ አመታት በፊተ እና በዚህ ዘመን በሚዘመሩ መዝሙሮች መካከል የምታያቸው ጉልህ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

ከሀያ አመት በፊት እና አሁን ያለው ችግራችን የዘማሪዎች ብቻ ሳይሆን የቤተክርስትያንም ጭምር ነው። ያም ምንድን ነው? በእግዚአብሔር ፊት ግዜ አናጠፋም፣ በኳየርም ሆነ በሶሎ አገልግሎት ሰፋ ያለ የጸሎት ግዜ አንወስድም። ስለዚህ አጥብቄ የምናገረው ነገር ቢኖር መንፈሳዊ ስራ ለመስራት በመንፈስ መሆን አለብን ከዚህ ውጭ ሌላ መንገድ የለም። የማይጸልይ ሰባኪ፣ የማይጸልይ ዘማሪ ፑልፒት ላይ የተሳካ አግልግሎት ያገለገለ ሊመስለው ይችላል ለህዝቡ ግን ቀሪ ነገር ከሌለው ፍሬ አይኖረውም። እንግዲህ በኔ አስተሳሰብ የማይጸልይ ሰባኪም ሆነ ዘማሪ መድረክ ላይ ባይቆም እመርጣለሁ፣ ቤተክርስቲያንም የጾም ጸሎትን አዋጅ ማወጅ አለባት። ይህን ስል ግን እንዳይረሳ የማስገነዝበው ነገር ቢኖር የሚጸልይ ሰባኪ፣ ወይንም ዘማሪ፣ እንዲሁም ጾም ጸሎት የሚያውጅ ቤቴክርስትያን የለም ማለቴ አይደለም፤ እንግዲህ በዱሮውና በአሁኑ መካከል ያለው ጉልህ ልዩነት ሌላ ነገር አይደለም በጌታ ፊት በመሆን ግዜን የማጥፈቱ ጉዳይ ነው። በአሁኑ ግዜ ያለውን የዝማሬ አገልግሎት ስንመለከት ትልቁ ችግር የዘማሪዎቹ ብቻ አይመስለኝም ችግሩ ቤተክርስትያን ሀላፊነቷን አለመወጣትዋ፣ ለዘማሪያንም መስመር አለማሳየቷ ይመስለኛል።

  1. የመዝሙር አገልግሎት የደረሰበትን ደረጃ ስትመለከት እንደሚገባ አድጓል ትላለህ?

ወደ ኋላ ልመለስ እና መንፈሳዊ ነገር ካላደገ በእድሜ ብዛት ምንም የሚያድግ ነገር የለም። የመዝሙር አገልግሎት እንደሚፈለገው አድጓል ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልስን ለመመለስ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ሙዚቃውን ስንመለከት አድጓል፤ ምክንያቱም በሲኮርድ ይዘን በዲ የዘመርንበት ግዜ ነበረ፤ ስለዚህ ሙዚቃው በጣም አድጓል፣ ግን መዝሙር ሊያድግ የሚችለው መንፈሳዊ ነገራችን ሲያድግ ነው። መዝሙር እንዳያድግ ያደረገው የራሱ ችግሮች አሉት፤ የተሰጡ ዘማሪያን፣ እግዚአብሔር የለያቸውና የቀባቸው እንዳሉ ሁሉ ብዙም ባይሆኑ ዝማሬ ከገንዘብ ጋር ተያይዞአልና ይህ ጉዳይ ዘማርያንን ወደሌላ አቅጣጫ አነሳስቶ እንዳይወስድና ከዚህም የተነሳ ሰዎች ዘማሪ መሆንን ይመኙታል ብዬ እፈራለሁ። ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ የመዝሙሩና ያገልግሎቱ ባለቤት ቤተክርስትያን መሆንዋ መዘንጋት የለበትም። ይህንን ስልጣን አሁን አላይም መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተክርስትያን ሰጠ የሚለው ቃል መዘንጋት የለበትም፤ በሌላ በኩል ዘማሪያን መዝሙር አውጥተው ለቤተክርስቲያን ሰጥተው ዘማሪው የሚበላው ያጣበት ግዜ ነበር ስለዚህ በዚህ አቅጣጫ ደግሞ ቤተክርስቲያን በድላለች። ሌላው ያኮረፉ አግልጋዮችን ቤተክርስቲያን ትቀበላለች ግን ያ አገልጋይ እዛም ቤ/ክርስትያን አባል አይሆንም ግን በተለያየ ቤ/ክርስትያን ያገለግላል ይህ ደግሞ የአገልጋዩን ህይወት  ቤ/ክርስትያን ለመከታተል ያስቸግራታል፤ ስለዚህ የዘማሪ ህይወት ሲበረታም ሆነ ሲደክም የሚከታተለው የለም እንግዲህ ባጠቃላይ ለመዝሙር እድገት ከመንፈሳዊ እድገት በተጨማሪ ቤተክርስትያን ሃላፊነቷን መወጣት አለባት እላለሁ።

Read 940 times Last modified on Wednesday, 15 June 2022 10:50

Mahlet Institute of Worship and Music
“Committed to Excellence in Worship and Music”

©2021 All rights reserved.